የአውራ አምባ አመጣጥ ታሪክ
የአውራ አምባ ማህበረሰብ በአማራ ክልል ደ/ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ለሰው ልጆች ፍትህ፣ እኩልነት፣ ፍቅር፣ ሰላማዊ ኑሮና ብልጽግናን ለማረጋገጥ መሰረት ሊሆን የሚችል አስተሳሰብና አሰራርን ይዞ የቀረበው ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ማህበረሰቡ የሴቶች እኩልነትን በማረጋገጥ፣ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ችግር በማላቀቅ፣ ልጆችን በስነ-ምግባርና በትምህርት ኮትኩቶ በማሳደግ፣ መጥፎ አስተሳሰብና አሰራርን አስወግዶ መልካም አስታሰሰብና አሰራርን በማጎልበት፣ ለሁሉም የሰው ልጆች እኩል ክብር በመስጠት፣ ጠንካራ የስራ ባህልን በመፍጠር፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስወገድና በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሰማራት ለአካባቢው ህብረተሰብ፣ ለክልሉና ብሎም ለአገራችን ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
የአውራ አምባ ማህበረሰብ ለህብረተሰቡ ያበረከታቸው አስተዋፆዎች
1. ማህበረሰቡ በባህልና እሴቶች ዙሪያ የሰራቸው ስራዎች
1.1. የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ
ማህበረሰቡ ሴቶች ላይ ይፈጸሙ የነበሩ የተለያዩ ጥቃቶችን፣ የጉልበት ብዝበዛና የስነ-ልቦና ጉዳት በማስቆም የሴቶችን እኩልነት አረጋግጧል፡፡ ማህበረሰቡ ይህን ማረጋገጥ የቻለውም፡-
Ø ሴት ልጆች ከ18 ዓመት በታች ጋብቻ እንዳፈጽሙ በመደረጉ፣
Ø ሴቶች የራሳቸውን እጣ ፋንታ በራሳቸው እንዲወስኑና ሙሉ መብት ያላቸው በመሆኑ፣
Ø ከሚፈልጉት ወንድ ጋር ጋብቻ የመፈጸም ሙሉ መብት ያላቸው በመሆኑ፣
Ø ሴቶች ፆታን መሰረት ካደረገ የስራ ጫና እንዲላቀቁ በመደረጉ፣
Ø ወላድ እናቶች ከወለዱበት ቀን ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል እንክብካቤ እንዲያገኙ መደረጉ፣
Ø ወላድ እናቶች በወሊድ ጊዜ 3 ወር ረፍት የማግኘት መብት ያላቸው በመሆኑና ስራ ሲጀምሩ በሚችሉት ስራ እንዲመደቡ መደረጉ፣
Ø በአጠቃላይ ሴቶች በትምህርት፣ በስራ፣ በአመራር ሰጪነት፣ ንብረትን በማስተዳደር፣ ተወያይቶ ውሳኔ በመስጠት ወዘተ የእኩልነት መብታቸው የተጠበቀ ነው።
1. 2 ልጆችን በጥሩ ስነ–ምግባርና በትምህርት ኮትኩቶ በማሳደግ
ማህበረሰቡ በልጆች አስተዳደግ ላይ እየሰራቸው ካሉት ስራዎች መካከልም፡-
Ø ሁሉም ህጻናት ከ3 ዓመታቸው ጀምሮ የቅድመ-መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ ይደረጋሉ፡፡
Ø በቅድመ-መደበኛ ት/ት ቆይታቸው ፊደሎችን እንዲለዩና ጥሩ ስነ-ምግባር እንዲላበሱ ይደረጋል፡፡
Ø ህጻናት 7 ዓመት ሲሞላቸው ወደ መደበኛ ትምህርት እንዲገቡ ይደረጋሉ፡፡
Ø ልጆች ከትምህርት መልስ የሚኖራቸውን ጊዜ የጨዋታ፣ የጥናትና የስራ ጊዜ ብለው በማቀድ በእቅድ መመራትን ይለማመዳሉ፡፡
Ø ልጆች በቤተሰብ ውይይት ሀሳባቸውን በነጻነት በማቅረብና ውይይቱን የመምራት መብት አላቸው፡፡
Ø ልጆች በአቅማቸው ስራን ተለማምደው፣ የአደንዛዥ እፆችን ጉዳት አውቀው፣ ከደባል ሱሶች ነጻ ሆነው እንዲያድጉ የሚደረግበት ሁኔታ ተዘርግቷል፡፡
Ø “መብታችን ተጓድሏል” ብለው የሚያስቡ ከሆነ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ መብታቸው የሚከበርበት አሰራር ተመቻችቷል፡፡
Ø ማህበረሰቡ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በዲፕሎማና ከዚያ በላይ የት/ት ደረጃ 88 ወጣቶችን በጥሩ ስነ-ምግባር አስተምሮ ለሀገር እድገት የበኩሉን አስተዋፆ አበርክቷል
1. 3 መጥፎ አስተሳሰብ፣ አነጋገርንና አሰራርን አስወግዶ በጎ አሰራሮችን በማጎልበት
Ø ማህበረሰቡ የሰው ልጆችን የሚጎዱ መጥፎ አሰራርና አነጋገርን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ መልካም አስተሳሰብን፣ አነጋገርንና አሰራርን አጎልብቷል፡፡
Ø ለአብነትም ማህበረሰቡ የራሱ ያልሆነን ገንዘብ ወድቆ ሲያገኝ ለባለቤቱ ተመላሽ ያደርጋል፡፡ በዚህም ረገድ፡-
ü ወድቀው የተገኙ በርካታ ሀብቶችን ወዲያውኑ ለባለቤታቸው ተመላሽ እያደረገ ይገኛል፡፡
ü ባለቤቱ ያልተገኘ ብር 6,261 ይህን ለሚመለከተው ኮሚቴ ገቢ ተደርጓል፡፡
ü ለኮሚቴ ገቢ ከተደረገው ውስጥ ብር 303 ከቀናት በኋላ ለባለቤቱ ተመልሶ ቀሪው ባለቤቱ ያልተገኘ ብር 5958.75 ለልማት እንዲውል ተደርጓል፡፡
1.4 ጥቅል ወገንተኛነትን በማጎልበት
Ø “ሁሉም የሰው ልጆች በሰውነታቸው ወንድም እህት ናቸው” በማለት በሰው ልጆች መካከል ባዕድ ዘመድ የሚለውን የተበጣጠሰ ወገንተኝነት አስቀርቷል፡፡
Ø የተበጣጠሰ ወገንተኝነትን በማስቀረት ጥቅልና ሙሉ የሰው ልጆችን ወገንተኝነት በመቀበል ሁሉንም የሰው ልጆች ወገኑ አድርጎ ይዟል፡፡
1.5 ሙሉ ሰላምን በማረጋገጥ
Ø ማህበረሰቡ ለሰው ልጆች ሙሉ ክብር በመስጠት ዘላቂ ሰላም እሚረጋገጥበትን ስልት በመንደፍ በማህበረሰቡ መካከል ሙሉ ሰላምን እንዲረጋገጥ አድርጓል፡፡
Ø ሙሉ ሰላምን ማረጋገጥ የቻለውም ለሚከሰቱት አለመግባባቶች መፍቻ ቁልፎችን መጠቀም በመቻሉ ነው፡፡
Ø አለመግባባቶችን የሚፈቱባቸው ቁልፎችም፡-
ü ችግሩ በሚፈጠርበት ወቅት በሚደረግ የእርስ-በርስ ውይይት፣
ü በየሁለት ሳምንቱ አንዴ በሚካሄደው ሰላምን ፍለጋ የቤተሰብ ውይይትና
ü ሶስተኛ ወገንን /ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴን/ በመጠቀም በሚደረጉ ውይይቶች ነው፡፡
Ø ማህበረሰቡ ሙሉ ሰላምን ለማረጋገጥ የተጠቀመባቸው ስልቶችም፡-
ü “ለሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ ሰው ልጅ ነው” በማለት ለሰው ልጆች ሙሉ ክብር መስጠት በመቻሉ፣
ü “ጠብን ከመሳል ይልቅ ፍቅርን እየሳልን ብንሄድ ጠብ ካለበት ተንኖ ይጠፋል” በማለት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳስ በመቻሉ፣
ü በውይይቱ በማመን እውነታውን አውጥተው መፍትሄ ላይ መድረስ ስለሚሰሩ፣
ü አሉባልታ /ሀሜት/ ቢከሰት በመነጋገር የመፍታት ልምድ በመኖሩ፣
ü ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ሰው በስሜታዊነት ጥፋቱን ወዲያውኑ ለማስተካከል ፈቃደኛ ባይሆን ራሱን የሚመረምርበት ጊዜ በመስጠት ችግሩን እንዲያርም ስለሚደረግ፣
Ø ማህበረሰቡ በአካባቢው ማህበረሰብ በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱ ከ20 በላይ የሚሆኑ ግጭቶችን የሽምግልና ስራ በመስራት አስታርቆ ሰላም እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
1. 6 ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስወገድ
ማህበረሰቡ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ናቸው ብሎ ያመነባቸው ቀጥሎ የተዘረዘሩት ሲሆኑ እነዚህን ድርጊቶችን ሙሉ በሙሉ እንዲወገዱ አድርጓል፡፡
Ø የጤና ችግር የሚያመጡ እንደ እንጥል ማስቆረጥ፣ ግግ ማስፈልፈል፣ የሴት ልጅ ግርዛትና የመሳሰሉት፤
Ø ኢኮኖሚያዊ ብክነት የሚያመጡ እንደ የተንዛዛ የለቅሶ ስርዓት፣ ሰርግና የተለያዩ አላግባብ የሆኑ የድግስ ስርዓቶች፤
Ø ማህበራዊ ቀውስን የሚያስከትሉ እንደ የልጅነት ጋብቻ፣ ጠለፋና ደባል ሱሶችን መጠቀምና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
1.7 ጠንካራ የስራ ባህልን በማረጋገጥ
Ø ማህበረሰቡ ጠንካራ የስራ ባህልን በማረጋገጥና በርትቶ በመስራት ለሌላው የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍልም ምሳሌነቱን እያሳየ ይገኛል፡፡
Ø ማህበረሰቡ ጠንካራ የስራ ባህልን ያዳበረውም፡-
ü “ከትንሽ ስራ በመነሳት ትልቅ መሆን ይቻላል” በማለት ስራ ሳይንቁ ለሁሉም ስራ እኩል ክብር ሰጥቶ መስራት በመቻሉ፣
ü ቀናትን አንዱን ከአንዱ ሳይለያይና ሳያበላልጥ ሁሉንም ቀናት በስራ ስለሚያውል፣
ü “የሴትና የወንድ ስራ” በማስቀረት ሁሉንም ስራ የሴቱም የወንዱም ማድረግ በመቻሉ፣
ü አባላት ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን አቀናጅተው በመተሳሰብ፣ በመደጋገፍና በመተባበር በጋራ የመስራት ልምድ በማዳበራቸው፣
ü ከስራ ጠባቂነት ወደ ስራ ፈጣሪነት በመሸጋገር ወደ ተለያዩ የማምረትና አገልግሎት ሰጭ የስራ ዘርፎች ለመሰማራት በመቻሉ፣
ü ልጆች ከቀለም ትምህርታቸው ጎን ለጎን እንደአቅማቸው የስራ ምንነትን ለምደው እንዲያድጉ በመደረጉ
1.8 ራሳቸውን መደገፍ ለማይችሉ ወገኖች ዋስትና በመሆን
Ø ለአረጋዊያንን፣ ድንገተኛ ችግር ላጋጠማቸው ወገኖችና ለተማሪዎች ድጎማ በማድረግ ዋስትናቸውን እየጠበቀ ይገኛል
Ø በዚህም ረገድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ
ü ለአረጋዊያን ብር 560,491.59
ü የባሰ ችግር ላጋጠማቸው የማህበረሰቡ አባላት ብር 256,322.15
ü ከማህበረሰቡ ውጭ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች ብር 324,212.50
ü ለተማሪዎች ብር 340,870.97 ድጋፍ ተደርጓል፡፡
Ø የስራ ዕድል ያላገኙ ወገኖችን የስራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ በኩል
ü ለ174 አባላቱ
ü ለ5 ቋሚና ከ30 በላይ ጊዚያዊ ቅጥር ሰራተኞችና
ü ለ27 በተለያየ ሙያ ለተመረቁ ወጣቶች የስራ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡
Ø በርካታ አቅመ–ደካሞችን ከአቅማቸው ጋር የሚመጣጠን ስራ በመስጠት እንደማንኛውም አባል እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
Ø በጤና ችግር ምክንያት ለዓመታት በስራ ገበታ ላልተገኙ አባላት የጥቅሙ እኩል ተካፋይ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
Ø ለአካባቢው ወጣቶች የሙያ ልምዶችን በማካፈል ራሳቸውን የሚመሩበት ልምድ እንዲያገኙ በማስቻል ስራ አጥነትን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡
2. በቱሪዝምና በትምህርት ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች
2. 1 በማህበረሰቡ ቱሪዝሙን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች
Ø የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በ2012 በጀት ዓመት ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንን፣ ወረዳዊ ፌስቲቫልን አውራ አምባ ላይ ሲያከብር በጀትና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡
Ø በእሴቶቹ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር በየደረጃው ካሉ አመራሮች ጋር ውይይቶች ተድርገዋል፡፡
Ø የባህል ቡድን በማቋቋም የማህበረሰቡን ባህልና እሴቶች ለማስፋት እንቅስቃሴ ተድርጓል፡፡
Ø ማህበረሰቡን በተለያዩ ሚዲያዎች የማስተዋወቅ ስራ ተጀምሯል፡፡
Ø አካባቢውን ሳቢና ማራኪ ለማድረግና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
Ø የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም
ü 1 ሬስቶራንትና 26 ማረፊያ ክፍሎች ተዘግጅተዋል፣
ü የ24 ሰዓት ኢንተርኔት አገልግሎት የማሟላት ስራ ተሰርቷል፡፡
ü ለኃይል መቆራረጥ ችግሮች አማራጭ የሶላር ፓናል ተዘርግቷል፡፡
ü የጉብኝት ቦታዎችን የማጽዳትና የማስዋብ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
2.2 በት/ት ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች
Ø ማህበረሰቡ ከፍተኛ መስዋትነትን በመክፈል ከ2002-2011 ዓ.ም ድረስ ብር 4,490,441.73 ወጪ በማድረግ ት/ቤቶችን በአቅራቢያው እንዲከፈቱ አድርጓል፡፡
Ø ማህበረሰቡ ት/ቤቶችን ለመክፈት የተነሳሳውም
ü የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግና
ü የተማሩ ሰዎችን ወደ ማህበረሰቡ በማቅረብ የልምድ መለዋወጫ ለማድረግ ነው፡፡














